በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የመልካም አስተዳደር አሰራርን ለማጠናከር ያለመ ስልጠና ተካሄደ
ነሃሴ 10፣ 2017
ልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ
በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማጎልበት ያለመ የመልካም አስተዳደር ስልጠና ተካሄደ። ስልጠናው ያተኮረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወጣው የቅሬታ አቀራረብ፣ ምርመራ፣ አወሳሰን እና የተጠያቂነት ስርዓት ደንብ ቁጥር 143/2015 ላይ ነው።
የኮሌጁ ዋና ዲን የሆኑት አቶ ተኩ ታዬ በመክፈቻ ንግግራቸው፣
"ይህ ስልጠና በኮሌጃችን የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመንና የደንበኞቻችንን እርካታ ለማሳደግ የምናደርገው ጥረት ወሳኝ አካል ነው"
ብለዋል።
የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማ የኮሌጁ አመራሮች፣ የዲፓርትመንት ተጠሪዎችና የስራ ክፍል ዳይሬክተሮች ስለደንቡ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን ማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል።
ስልጠናውን የመሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የመልካም አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ወረታ ናቸው። አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ደንብ ቁጥር 143/2015 የቅሬታ አቀራረብን ሂደት ከማቅለሉም ባሻገር፣ የምርመራ ሂደቱ ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚያስችሉ መርሆዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ውሳኔ አሰጣጡ በእውነታ ላይ የተመሰረተና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።




.