Announcement ወርቃማ ሰኞ "ለውጥን ማስተዳደር"

ወርቃማ ሰኞ "ለውጥን ማስተዳደር"

11th August, 2025

ወርቃማ ሰኞ

ልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ

በ"ወርቃማ ሰኞ"መድረክ

በየሳምንቱ ሰኞ በሚካሄደውና በጉጉት በሚጠበቀው "ወርቃማ ሰኞ" በተሰኘው የውይይት መድረክ ላይ የኮሌጁ ዋና ዲን የሆኑት አቶ ተኩ ታዬ "ለውጥን ማስተዳደር" በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ገለጻና ትንታኔ አቅርበዋል።

በንግግራቸውም ለውጥ በአንድ ተቋም፣ ማህበረሰብ ወይም ግለሰብ ህይወት ውስጥ ሊከሰት የሚችል የማይቀር ሂደት መሆኑን የገለጹት አቶ ተኩ፣ ለውጥን በስኬት ለማስተዳደር ቆስቃሽና መካች ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።

አቶ ተኩ እንዳብራሩት፣ ቆስቃሽ ሁኔታዎች ማለት ለውጥን የሚደግፉና እንዲከሰት የሚያደርጉ አዎንታዊ ሁኔታዎች ሲሆኑ፤ ለአብነትም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ የገበያ ፍላጎት ለውጥ እና የተሻለ አሰራርን የመፍጠር ፍላጎት ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል። በሌላ በኩል መካች ሀይሎች ለውጥን የሚቃወሙና ሂደቱን የሚያጓትቱ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የሰራተኞችን የስራ ልምድ፣ የሀብት እጥረት እና ለውጥን መፍራትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም አቶ ተኩ ንግግራቸውን ያጠቃለሉት ለውጥን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል በማብራራት ነው። "ለውጥ የአንድ ጊዜ ክስተት ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው" ያሉት ዲኑ፣ የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል ቀጣይነት ያለው ክትትል፣ ግምገማና ማስተካከያ ማድረግ፣ እንዲሁም የሰራተኞችንና የተገልጋዮችን አስተያየት መቀበልና ማስተናገድ ወሳኝ መሆኑን በማሳሰብ ነው።

መድረኩ በቀጣይ ሳምንት በሌላ አዲስና ወቅታዊ ርዕስ እንደሚቀጥልም አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with