በ"ወርቃማ ሰኞ" መድረክ የድርጅት ባህል በድርጅቶች ስኬት ላይ ያለው ሚና
ልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ
በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ በተካሄደው "ወርቃማ ሰኞ" መድረክ ላይ የድርጅት ባህል በአንድ ድርጅት ስኬት ላይ ስላለው ወሳኝ ሚና ሰፊ ትንተና ቀርቧል። መድረኩ በአንድ ድርጅት ውስጥ የሚፈጠረው የስራ ባህል በሰራተኞች ምርታማነትና ስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው አሳይቷል። በኮሌጁ የሆቴል እና መስተንግዶ ዲፓርትመንት አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ያሬድ አባተ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ሁለት ዋና ዋና የድርጅት ባህሎች መኖራቸው ተብራርቷል- ጤናማ እና ጤናማ ያልሆነ የድርጅት ባህል።
ጤናማ ያልሆነ የሥራ አካባቢ በሰራተኞች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድርና ጤናማ ያልሆኑ ልማዶች፣ ፖሊሲዎች እና የአመራር ዘይቤዎች የሚስተዋሉበት ሁኔታ ነው። ይህ አይነቱ ባህል የሰራተኛ ፍልሰት እንዲጨምር፣ በሰራተኞች መካከል ጤናማ ያልሆነ ፉክክርና የቢሮ ወሬ እንዲሰፋ ምክንያት ከመሆን ባሻገር ሰራተኞች እውቅና እና ሽልማት ስለማያገኙ የሞራል ዝቅጠት ይገጥማቸዋል። እነዚህ ባህሪያት የሰራተኞችን ምርታማነት በመቀነስ የድርጅቶችን አጠቃላይ አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራሉ።
በሌላ በኩል፣ ጤናማ የድርጅት ባህል የሰራተኞችን ተሳትፎ፣ ደስታ እና ምርታማነት በማሳደግ የድርጅቱን የገቢና የአገልግሎት ዕድገት ያፋጥናል። ጤናማ የሥራ ባህል ለመፍጠር ወሳኝ የሆኑት ነገሮች ግልጽ ግንኙነትና የጋራ እሴቶች መኖር፣ ትብብርና የቡድን ስራን ማበረታታት፣ ለሰራተኞች ቀጣይነት ያለው የሙያ ዕድገት ዕድሎችን መስጠት እንዲሁም ፍትሃዊ እውቅናና ሽልማት መስጠት ናቸው።
የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ተኩ ታዬ ፣ ጤናማ የድርጅት ባህል የአገልግሎት ጥራትን ከማሳደግ ባለፈ፣ ማህበራዊ ተሳትፎና ሀላፊነትን በመወጣት ለዘላቂ ስኬት ቁልፍ መሆኑን አሳሰቡ።





.